ስለኢትዮጵያ ይሁዲዎች
የይሁዳውያን ሰፈራ ታሪክ በኢትዮጵያ
ይሁዳውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በዚያች አገር መኖር የጀመሩበት ወቅት፦ በኢትዮጵያ የይሁዳውያን ታሪክ እስከ 14ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል ሲተላለፍ ከነበረው በስተቀር በጽሑፍ አልተያዘም (አልተጻፈም)። ስለሆነም የኢትዮጵያ አይሁዳውያን ምንጭ (መሠረት) ወደ ኢትዮጵያ የገቡበት ጊዜ መቼ እንደነበረ አይታወቅም። ይህንን በተመለከተ ለዓመታት ያህል የሚነገሩ ግምቶች አሉ።
1. የኢትዮጵያ ይሁዳውያን - ቤተ እስራኤል በመባልም የሚታወቁት - ምንጫቸው ከተሰደዱት የዳን ነገድ ወይም ከዚያ በፊት የእስራኤል ነገሥታት ከተለያዩበት ጊዜ ጀምሮ ነው።
በምድረ ኩሽ (ኢትዮጵያ) የተሰደዱ ይሁዳውያን እንዳሉ በመጽሐፍ ቅዱስ በነቢያት ተጽፏል። በዚያን ጊዜ ታላቅ የኃይል ሥራ ይሠራል። እርሱም "በአሦርና በግብፅ፣ በጳጥሮስ አገራት፣ በኩሽ፣ በኢላም፣ በባቢሎንና በሐማት እንዲሁም በባሕር ዳርቻዎችና በደሴቶች የሚኖሩትን የቀሩትን ወገኖቹን ወደ አገራቸው ይመልሳል"። በዚህም ወቅት በዓለም ተበትነው የሚገኙትን እስራኤላውያንንና የይሁድ ወገኖችን ከዓለም አራት ማዕዘናት ሰብስቦ በመውሰድ ለዓለም ሕዝቦች ምልክት የሚያሳይበት ተግባር ይሆናል። (ኢሳይያስ ምዕራፍ 11 ቁጥር 11 እስከ 12)።
የኢሳይያስ መጽሐፍ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላውያን ከዳን ነገድ ናቸው እንደማይል መጥቀስ ያስፈልጋል። ከዳን ነገድ መሆናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ9ኛው ክፍለ ዘመን በኤልዳድ ሀዳኒ ጽሑፎች ሲሆን፣ ቆይቶም እንደ ራድባዝ ባሉ የራባናት (ካህናት) ምንጮች (ጽሑፎች) ተጠቅሷል። የቀድሞው የእስራኤል ዋና ራቢ፣ ራብ ዖባዲያ ዮሴፍ የኢትዮጵያ አይሁዳውያን በእርግጥ ይሁዳውያን ናቸው ብለው ሲወስኑ እነዚህን የተጠቀሱ ነጥቦች መሠረት በማድረግ ነው።
2. የኢትዮጵያ አይሁዳውያን ምንጭ (መሠረት) ከክርስቶስ ልደት በፊት በ7ኛው ክፍለ ዘመን ከግብፅ ከተሰደዱት ወገኖች እንደሆነ ይገመታል። ለስደታቸውም ምክንያት በውስጣቸው በነበረ አለመስማማት ወይም በውጫዊ ዘረኝነት ምክንያት በደረሰባቸው ችግር ነው።
የዚህ ግምታዊ አባባል መሠረት በኢትዮጵያ አይሁዳውያን ማኅበረሰብ ውስጥ የሚነገረው ታሪክና በይሁድ ተመራማሪዎች የሚደገፍ ሲሆን፤ ይህም በግብፅ ቤብ (ኤሌፋንቲን) (beb/Elephantine) ይባሉ ከነበሩት የጥንት ይሁዳውያን ባህል ጋር የኢትዮጵያ አይሁዳውያን ባህል ስለሚመሳሰል ነው።
3. የኢትዮጵያ አይሁዳውያን አባቶች ከግብፅ ሳይሆን የተሰደዱት ብዙና ትልቅ ትርጉም ካለው ከደቡብ ዓረብ (የመን) ነው የሚል ሌላ ግምትም አለ። ተመራማሪዎች ይህንን ግምት የሚሰጡት በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን የጂኦግራፊያዊ ቅርበት እንዲሁም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ5ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበረውን የንግድ ልውውጥና የባህል ግንኙነት መረጃዎችንና መሠረቶችን በማድረግ ነው።
4. በኢትዮጵያ ብሔራዊ አባባል፣ ይሁዳውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ወይም የመጡት በሰለሞን ዘመን ነው። ይህ አባባል በሰለሞንና በንግሥተ ሳባ መካከል የነበረውን ግንኙነት፣ በዚህም ግንኙነት ምክንያት በኢትዮጵያ ያደገው ልጃቸው ምኒልክ መወለዱ በመጽሐፍ ቅዱስ (ተያያዥ ታሪኮች) መገለጹ የሚደግፈው ነው። ምኒልክ ካደገ በኋላ አባቱን ንጉሥ ሰለሞንን ለመጠየቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። የኢየሩሳሌም ቆይታውን አብቅቶ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ፣ ከእስራኤል ነገዶች የተውጣጡ ተወካዮች አጅበውት እንዲሄዱ ስለተደረገ አብረውት ሄዱ። የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤል ምንጭም ከዚህ የተነሳ ነው። ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ አባባል "ክብረ ነገሥት" ከተባለው የኢትዮጵያ መጽሐፍ የተገኘ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቃል ታሪክ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ቤተ እስራኤልም ዘንድ የታወቀ ነው።
5. የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤል ከጥንት የይሁድ ማኅበረሰብ የተገኙ ሳይሆኑ፣ "አገው" ከሚባሉት የኢትዮጵያ ነገዶች መካከል በ14ኛው እና በ15ኛው ክፍለ ዘመን የይሁድነት ሃይማኖት የተቀበሉ ናቸው። ይህ ግምታዊ አባባል በአንዳንድ ተመራማሪዎች ባለፉት አሥርተ ዓመታት የተነገረ ሲሆን፤ ምክንያቱም ስለ ኢትዮጵያ ይሁዳውያን መኖር፤ የአገሪቱ መሪዎች መናገር የጀመሩት ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በመሆኑ ነው። ይህ አባባል በኢትዮጵያ ይሁዳውያን ዘንድ ተቀባይነት የሌለው (የተገፋ) ነው። እንዲሁም አብዛኞቹ ተመራማሪዎች የኢትዮጵያ ይሁዳውያን የክርስትና ሃይማኖት ወደ አገሪቱ ከመግባቱ በፊት ጀምሮ እዚያ እንደነበሩ ይናገራሉ።
ከጥንት እና ከመካከለኛው ዘመን መጀመሪያ የተገኙ ማስረጃዎች።
የአክሱም መንግሥት (ከ1ኛው እስከ 7ኛው ክፍለ ዘመን) በአሁኑ ሰሜን ኢትዮጵያና ኤርትራ ተዘርግቶ የነበረ ሲሆን፣ በጥንቱ ዓለም ከነበሩት ታላላቅ መንግሥታት አንዱ ነበር። በይፋዊ ቋንቋው – ግዕዝ – ከይሁዳውያን አረማይክ የተወሰዱ ቃላት ይገኛሉ፣ ይህም በአክሱም መንግሥት ላይ የነበረውን የይሁዳውያን ተጽዕኖ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። በአራተኛው ክፍለ ዘመን፣ የአክሱም ነገሥታት ክርስትናን ተቀብለው የሀገሪቱ ይፋዊ ሃይማኖት ሲያደርጉት፣ በአንጻሩ በስተምሥራቅ በቀይ ባሕር ማዶ የምትገኘው ጎረቤቷ የሒምያር (የየመን) መንግሥት ነገሥታት ወደ ይሁዲ እምነት ተለወጡ፤ ይሁድነትም የዚያ መንግሥት ይፋዊ ሃይማኖት ሆነ። በስድስተኛው ክፍለ ዘመን፣ በአክሱምና በሒምያር መካከል እንደ ይሁድና እና ክርስትና ሃይማኖታዊ ግጭትም በሚታይ ረጅም ውዝግብ ምክንያት፣ የአክሱም መንግሥት ሒምያርን ድል በማድረግ ክርስቲያን ንጉሥ አነገሠባት።
የአክሱም መንግሥት በሰባተኛውና በስምንተኛው ክፍለ ዘመን ቀስ በቀስ እየተዳከመ ሄደ። በይሁዳውያንም ሆነ በክርስቲያን ወገን ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ወግ መሠረት፣ መንግሥቱ የተሸነፈውና የአክሱም ከተማ ያጠፋችው ከጌዴዎን ሥርወ መንግሥት የተወለደች ዮዲት (ጉዲት) በተባለች ይሁዳዊት ንግሥት እጅ ነው። በዓሥረኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ ምንጮች በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ ግዛቶችን የተቆጣጠረች ንግሥት መኖሯን ቢጠቅሱም፣ ስለ እሷ ዝርዝር መረጃ ግን አይሰጡም።
በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን በመካከለኛው ምስራቅ የተለያዩ የይሁዳውያን ማኅበረሰቦችን የጎበኘው ኤልዳድ አዳኒ፣ ትውልዱ ከዳን ነገድ እንደሆነና ከአሥሩ ነገዶች መካከል ከሆኑ ሌሎች ነገዶች ጋር በኩሽ ምድር እንደሚኖር ተርኳል። በተጨማሪም እነዚህ ነገዶች "እስከ ዛሬ ድረስ ከኩሽ መንግሥታት ልጆች ጋር ይዋጋሉ" ሲል ገልጿል። በ12ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ተጓዥ ቢንያሚን መቱደላ በዓደን ምድር በከፍተኛ ተራራዎች ላይ ስለሚኖሩ ነጻ ይሁዳውያን ተርኳል፤ እነዚህም ወደ ሉቢያ (ምናልባትም ኑቢያ) ምድር በመውረድ ከክርስቲያን ነዋሪዎቿ ጋር እንደሚዋጉ ጠቅሷል። እነዚህ ታሪኮች ስለ የኢትዮጵያ ይሁዳውያን (ቤተ እስራኤልን) እንደሚያመለከቱ የሚጠቁሙ ምሁራን አሉ።
የጌዴዎን ሥርወ መንግሥት (የጌዴዎኖች መንግሥት)
ስለ ይሁዳውያን ስደተኞች ታሪክ ያለው የተለመደ ትረካ፣ በይሁዳ የነበረው የይሁዳውያን አስተዳደር በሮማውያን እጅ ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁኗ የእስራኤል መንግሥት ምስረታ ድረስ፣ ይሁዳውያን ለ2,000 ዓመታት ያህል በሌሎች ሥልጣን ሥር እንደ አናሳ ማኅበረሰብ እንደኖሩ ይነገራል። በተግባር ግን በጥንት ዘመንና በመካከለኛው ዘመን መጀመሪያ ላይ በስደተኛ ይሁዳውያን ነጻነት የታየባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች ነበሩ፤ ነገር ግን እስከ ዘመናዊው ዘመን ድረስ ነጻነቷን ጠብቃ የቆየችው ብቸኛ የይሁዳውያን ማኅበረሰብ የቤተ እስራኤል ማኅበረሰብ ነች። የዚህ ማኅበረሰብ አባል ከክርስቲያኑ የሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ጋር ያደረገው የጀግንነት ውጊያ ዜና በሰፊው ይሁዳዊ ዓለም ተሰራጭቶ ለሁሉም የእስራኤል ስደተኞች የብርታት ምንጭ ሆኖ አገልግሏል። በክርስትና ወይም በእስልምና አገዛዝ ሥር ለኖሩትና በተደጋጋሚ ለተለያዩ አዋጆችና ገደቦች ይጋለጡ ለነበሩት የአውሮፓና የመካከለኛው ምስራቅ አይሁዶች፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የራሳቸው ነገሥታትና ጦር ያላቸው፣ ከክርስቲያን መንግሥት ጋር በጀግንነት የሚዋጉ ይሁዳውያን መኖራቸውን ማወቃቸው ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሮላቸው ነበር። በአውሮፓና በመካከለኛው ምስራቅ የነበሩ ይሁዳውያን ዓይናቸውን ወደ ኢትዮጵያ ይሁዳውያን በማቅናት፣ በዚያ የይሁድ መንግሥት መኖሩን እንደ ተስፋ ምንጭ ይመለከቱት ነበር።
በ13ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በኢትዮጵያ ደጋማ ክፍል ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ የሰለሞናዊው የክርስቲያን ሥርወ መንግሥት ወደ ሥልጣን መጣ። በሚቀጥሉት ዓመታትም ግዛቱን የቤተ እስራኤል ማኅበረሰብ ወደሚኖርባቸው አካባቢዎች አስፋፋ። በሰለሞናዊው ሥርወ መንግሥት ቤተ መንግሥት ውስጥ የነገሥታቱን ታሪክ የመመዝገብ ኃላፊነት የነበራቸው ጸሐፍት ነበሩ፤ በዚህም ምክንያት የሰለሞናዊው መንግሥት በማኅበረሰቡ ላይ ያደረጋቸው የጦርነት ዘመቻዎች ዝርዝር መግለጫዎች ሊደርሱን ችለዋል። ስለ ውጊያዎቹና ማኅበረሰቡ በተወሰኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ ስለነበረው አገዛዝ የሚገልጹ ተጨማሪ ዘገባዎች በዚያ ዘመን ኢትዮጵያን በጎበኙ የመካከለኛው ምስራቅ ሙስሊሞችና የአውሮፓ ክርስቲያኖች ጽሑፎች ውስጥ ይገኛሉ። እንዲሁም በግብፅና በእስራኤል ይኖሩ በነበሩ ይሁዳውያን ጽሑፎች ውስጥም ይገኛሉ። እነዚህ ይሁዳውያን ለሐጅ የመጡ ወይም በጦርነት ተማርከው በባርነት የተሸጡ ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ የተረኩ የኢትዮጵያ ይሁዶዎችን አግኝተው ነበር።
በኢትዮጵያ ስለነበረው የይሁዳውያን መንግሥት እንዲሁም ማኅበረሰቡ ከሰለሞናዊው መንግሥት ጋር ስላደረገው የጀግንነት ውጊያ የሚገልጹ ትረካዎች በማኅበረሰቡ አባላት ዘንድ በቃልም ሲተላለፉ ቆይተዋል። በማኅበረሰቡ ባህላዊ ትውፊት መሠረት፣ መንግሥቱ "የጌዴዎን ሥርወ መንግሥት" ተብሎ ይጠራል፤ ይህም መንግሥቱን ያስተዳድሩ በነበሩትና "ጌዴዎን" ተብለው በሚጠሩት ነገሥታት ስም የተሰየመ ነው። በእርግጥም፣ የማኅበረሰቡ አገዛዝ በነበረበት ወቅት ከተጻፉ ምንጮች መካከል፣ ከሌሎች ስሞች በተጨማሪ "ጌዴዎን" የሚባሉ መሪዎች ይጠቀሳሉ።
በቤተ እስራኤል ታሪክ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ ከሆኑት ክስተቶች አንዱ ከ1414 እስከ 1429/30 ዓ.ም የገዛው የሰለሞናዊው አፄ ይስሐቅ የጦር ዘመቻ ነው። ከዚህ የጦር ዘመቻ በፊት ማኅበረሰቡ ጸለምት፣ ሰሜን፣ ወገራ እና ደምቢያን ያካተተ ሰፊ ግዛት ያስተዳድር ነበር። ይስሐቅ ሰራዊቱን ወደ ወገራ በማምራት የቤተ እስራኤልን ጦር ድል አደረገ። ማኅበረሰቡ በደምቢያና በወገራ የነበረውን ለም መሬት ቀምቶ ለደጋፊዎቹ አከፋፈለ፤ እንዲሁም በአሸነፈባቸው አካባቢዎች ክርስትናን ለማስፋፋትና አገዛዙን ለማጽናት አብያተ ክርስቲያናትን መሠረተ። እንዲያውም እንዲህ ሲል አወጀ፦ "በክርስትና ጥምቀት የተጠመቀ የአባቶቹን ርስት ይወርሳል። ካልሆነ ግን ከአባቶቹ ርስት ይነቀላል፣ ፈለሴ (ስደተኛ/መሬት የሌለው) ይሆናል።" ይህም ማለት ከማኅበረሰቡ አባላት መካከል ክርስትናን ያልተቀበለ መሬቱን ያጣል ማለት ነው። ከጦርነቱ በኋላ የይሁዳውያን አስተዳደር በሰሜን ተራሮችና በጸለምት አውራጃ ብቻ ተወስኖ ቀረ።
በጦርነቱ ሽንፈት እና ንጉሠ ነገሥቱ በይሁዳውያን ሃይማኖት ላይ በጸኑት ላይ በጣሉት አዋጅ ምክንያት፣ የማኅበረሰቡ ቀጣይነት ትልቅ አደጋ ተጋርጦበት ነበር። የማኅበረሰቡ ትውፊት እንደሚተርከው፣ ለዚህ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት በሁሉም ዘመን ከነበሩት ታላላቅ መንፈሳዊ መሪዎች አንዱ የሆኑት አባ ጽብራ እና ደቀ መዝሙራቸው አባ ጸጋ አምላክ ተነሱ። እነዚህ መሪዎች ማኅበረሰቡ በሚኖርባቸው የተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር እንደ መንፈሳዊ መምህራን በማገልገል የይሁድ ሃይማኖት እንዳይጠፋ ተጉ (አደረጉ)። ለአባ ጸብራ የተለያዩ የሃይማኖት ድርሳናት፣ ጸሎቶች እና የማኅበረሰቡ ሕግጋት (ሃላኾት) ይጠቀሳሉ፤ ከእነዚህም መካከል በኢትዮጵያ ይሁዳውያን እና ይሁድ ባልሆነው ማኅበረሰብ መካከል አካላዊ መለያየትን የፈጠሩ የንጽሕና ሕግጋት ይገኙባቸዋል። ይህም የሃይማኖት ድንበሮችን በማጠናከር ማኅበረሰቡ ከሌላው ማሕበረሰብ ጋር እንዳይቀላቀልና እንዳይጠፋ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።
በ1529 (እ.ኤ.አ) ደቡብና ደቡብ ምስራቅ ከሚገኘው የሰለሞናዊው መንግሥት ግዛት ሙስሊሞችን በአንድነት ያስተባበረው መሪ አህመድ ቤን ኢብራሂም አል-ጋዚ (አህመድ ግራኝ)፣ የሰለሞናዊውን መንግሥት አብዛኛውን ግዛት የተቆጣጠረበትን የድል ጉዞ ጀመረ። በዚያ ወቅት በሰሜን ተራሮች (ሰሜን) እምብርት ላይ የአካባቢውን ይሁዲዎች በቁጥጥሩ ሥር ያደረገ የሰለሞናዊው መንግሥት ምሽግ ነበር። የሰሜን ይሁዲዎች የሙስሊሙ ጦር ምሽጉን እንዲቆጣጠር ቢረዱም፣ በኋላ ላይ ግን በ1542 (እ.ኤ.አ) ወደ አፄ ገላውዴዎስ ድጋፍ ተመለሱ።
በዚያው ወቅት፣ የፖርቹጋል ጦር ክፍል የሰለሞናዊውን ጦር ከሙስሊሞች ጋር ለሚያደርገው ውጊያ ለማገዝ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ይዞ መጣ። የባይዳ ይሁዳዊ ገዥ፣ የባይዳን አምባ ከሙስሊሞች እጅ በጋራ ለመንጠቅ ለሰለሞናዊውና ለፖርቹጋል ጦር አዛዦች ሐሳብ አቀረበ፤ በዚያው መሠረትም ተከናወነ። በኋላ ላይ የሰለሞናዊውና የፖርቹጋል ጦር በሙስሊሞች ተሸንፈው ሲያፈገፍጉ፣ በጌዴዎኖች መንግሥት እምብርት ወደምትገኘው ባይዳ ተጠለሉ፤ በዚያም ለወይና ደጋ ውጊያ ተዘጋጁ። በዚህ ውጊያ የሙስሊሙ መሪ የተገደለ ሲሆን፣ ውጤቱም የሰለሞናዊው መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ላይ የነበረውን የበላይነት እንደገና እንዲያገኝ አስቻለው።
የሰለሞናዊው መንግሥት በጦርነቱ ምክንያት መዳከሙ በደቡባዊ ግዛቶቹ ላይ የጸጥታ መደፍረስ አስከተለ። የሰለሞናዊው ነገሥታት ዋና ከተማቸውን የሚመሠርቱበት የተሻለና አስተማማኝ ቦታ መፈለግ ጀመሩ፤ በመጨረሻም ከጣና ሐይቅ በስተሰሜን ምስራቅ ያለውን አካባቢ መረጡ። ይህ ቦታ የቤተ እስራኤል ማኅበረሰብ በሚኖርበት እምብርት ላይ የሚገኝና ከጌዴዎኖች መንግሥት ብዙም የማይርቅ ነበር። በዋና ከተማው ዙሪያ ያሉትን ግዛቶች በሙሉ በቁጥጥር ሥር የማድረግ ፍላጎት፣ የሰለሞናዊው ነገሥታት በዚያ ወቅት በቤተ እስራኤል ማኅበረሰብ ላይ ለሚያደርጉት ተከታታይ የጦርነት ዘመቻዎች ዋነኛው ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።
በአፄ ሠርፀ ድንግል (ከ1563–1597 የገዙ) ዘመነ መንግሥት በሰሜን ይሁዳውያን መሪዎች ማለትም በረዳኢ፣ በከለፍ እና በጎሸን ላይ ተከታታይ የጦር ዘመቻዎች ተካሂደው ነበር፤ ንጉሡም ምሽጎቻቸውን ተቆጣጠሩ። በከለፍ ምሽግ ላይ በተደረገው ውጊያ፣ ይሁዳውያኑ ከምሽጉ አናት ላይ ታላላቅ ድንጋዮችን በሰለሞናዊው ወታደሮች ላይ ያንከባልሉ ነበር። ሆኖም የሰለሞናዊው ጦር በወቅቱ በኢትዮጵያ አዲስ የነበሩትን መድፎች በመጠቀሙ ውጊያውን ማሸነፍ ቻለ። በዚህ ውጊያ ላይ አንዲት የማኅበረሰቡ አባል የፈጸመችው የጀግንነት ተግባር በታሪክ ይዘከራል፤ ይህ ድርጊት በራሱ በሠርፀ ድንግል የዜና መዋዕል ጸሐፊ (በጦርነቱ ላይ በነበረው) ተመዝግቧል። ዮሴፍ ሃሌቪ ጽሑፉን እንዲህ ተርጉሞታል።
በዚያን ጊዜ አንዲት የተማረከች ሴት ላይ አስደናቂ ነገር ተፈጠረ፤ ማራኪዋ እጇን ከእጁ ጋር አስሮ እየመራት ነበር። በታላቅ ገደል አፋፍ ላይ ሲጓዙ ባየች ጊዜ፦ "ጌታ ሆይ እርዳኝ!" ብላ ጮኸች። ራሷን ወደ ገደሉ ወረወረች፤ ያንንም እጇን ያለፍላጎቷ ከእጁ ጋር አስሮ የነበረውን ሰው አብራው ሳበችው። በክርስቲያኖች መካከል ብቻዋን ከመሆን ይልቅ ለሞት ራሷን አሳልፋ የሰጠችው የዚች ሴት ጀግንነት ምንኛ ድንቅ ነው! በእርግጥ ይህንን ያደረገችው እሷ ብቻ አይደለችም፣ ሌሎች ብዙ ሴቶችም እንዲሁ አድርገዋል፤ ነገር ግን እኔ ድርጊቷን ያየሁ የመጀመሪያዋ ሴት እሷ ነበረች1።
በውጊያዎቹ መሸነፍ ምክንያት ረዳኢ እጁን ሰጠ፤ በምርኮም ተወሰደ። የእርሱም ዘውዶች በሰለሞናዊው ጦር ተዘረፉ። የጎሸን ምሽግ በሰለሞናዊው ጦር በተያዘ ጊዜ፣ ጎሸን ራሱን ከከፍተኛ ገደል ላይ በመወርወር ሕይወቱ አለፈ። ጌዴዎን ግን ማምለጥ የቻለ ሲሆን፣ በሚቀጥሉትም ዓመታት በሰሜን (ሰሜን ተራሮች) የነበረውን አገዛዝ አስጠብቆ መቆየት ችሏል።
አፄ ሠርፀ ድንግል የጌዴዎንን እህት ሓረጉን አግብተው ነበር፤ ለእነርሱም ያዕቆብ የተባለ ልጅ ተወለደላቸው። ያዕቆብም ለጥቂት ጊዜ የሰለሞናዊው መንግሥት ንጉሠ ነገሥት ሆኖ ተሾመ። የሰለሞናዊው መኳንንት በእርሱ ላይ በቆሰቆሱት ሴራ ምክንያት፣ ያዕቆብ በሰሜን ወደሚገኘው አጎቱ ጌዴዎን ለማምለጥ ቢሞክርም ተይዞ በግዞት ተላከ፤ በእርሱም ምትክ አፄ ዘድንግል ነገሡ። መኳንንቱ በዘድንግል ላይም በማመፃቸው ንጉሡ በጦርነት ተገደሉ፤ በዚህም ያዕቆብ ወደ ሥልጣን ተመለሰ። ሆኖም በዚያን ጊዜ የአፄ ልብነ ድንግል ቅድመ-የልጅ ልጅ የሆኑት ሱስንዮስ ሌላው የሥልጣን ተፎካካሪ ሆነው ተነሱ። ያዕቆብ በጦርነት ተገደለ፣ ሱስንዮስም ወደ ሥልጣን መጡ። የጌዴዎን እህት የሓረጉና የአፄ ሠርፀ ድንግል ልጆች የሆኑት ሌሎች ሁለት ወንድማማቾች በጌዴዎን እርዳታ የሰለሞናዊውን ሥልጣን ለመመለስ ቢሞክሩም፣ ሱስንዮስ ማርኮ በሞት ቀጣቸው።
ጌዴዎን ሱስንዮስ በቤተሰቡ ላይ የፈጸመውን ግድያ አልረሳም ነበር፤ በመሆኑም በንጉሡ ላይ የሚነሱ አማፂያንን ለመርዳት አመቺ ሁኔታዎችን ሁሉ ይጠቀም ነበር። በሌላ በኩል ሱስንዮስ በጌዴዎን ላይ ተከታታይ የጦር ዘመቻዎችን አደረገ። ጌዴዎን እጁን በሰጠበት የመጀመሪያው ዘመቻ ማግስት፣ ሱስንዮስ በደምቢያ አካባቢ የሚኖሩ ይሁዲዎችን በግድ ወደ ክርስትና ለመለወጥ ሞከረ፤ በተመሳሳይ ጊዜም በሰሜን፣ በወገራ፣ በበለሳና በጃንፋንከራ በሚኖሩ ይሁዳውያን ላይ ጭፍጨፋ ፈጸመ። በሁለተኛው የጦር ዘመቻ ግን ይሁዳውያኑ ድል አደረጉ፤ በዚህም ምክንያት ሱስንዮስ የሰሜን ተራሮችን ሳይቆጣጠር በዙሪያው ጥበቃ ለማቆም ተገደደ። ጌዴዎን ከሰለሞናዊው ጦር ጋር ባደረገው ውጊያ ከተገደለ በኋላ፣ ሱስንዮስ በ1626 (እ.ኤ.አ) ሌላ የጦር ዘመቻ በማካሄድ የጌዴዎኖችን መንግሥት ለመጨረሻ ጊዜ ድል በማድረግ ተቆጣጠረ።
J. Halévy, La guerre de Sarṣa Děngěl contre les Falachas. Texte Éthiopien. Extrait des Annales de Sarṣa Děngěl, roi d’Éthiopie (1563-1597). Manuscrit de la Bibliotheque Nationale nº 143. Fol. 159 rº, col. 2 – fol. 171 vº, col. I, Paris 1907, p. 86.
ከጎንደር ዘመን እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ።
የሱስንዮስ ልጅ አፄ ፋሲለደስ (ከ1632–1667 የገዙ) መቀመጫቸውን በጎንደር በማድረግ በዚያ ቤተ መንግሥታቸውን አነጹ። ከእሳቸው ዘመን ጀምሮ እስከ አፄ ቴዎድሮስ (ከ1855–1868 የገዙ) ዘመነ መንግሥት ድረስ ጎንደር የሰለሞናዊው መንግሥት ዋና ከተማ ሆና አገልግላለች። በፋሲለደስ ቤተ መንግሥት ዙሪያ ሌሎች የነገሥታት መኖሪያዎች ተገነቡ፤ በከተማዋና በአካባቢዋም ለሰለሞናዊው መኳንንት የሚያገለግሉ አብያተ ክርስቲያናትና የተለያዩ ሕንፃዎች ተሠሩ። በዚያን ጊዜ ብዙዎቹ የቤተ እስራኤል ማኅበረሰብ አባላት በግንባታ ጥበብ የታወቁ ስለነበሩ፣ በንጉሣዊው ቅጥር ግቢና በከተማዋ የሕዝብ መገልገያ ሕንፃዎች ግንባታ ላይ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል። ጎንደር ከተመሠረተች በኋላ ባሉት ዓመታት ማኅበረሰቡ የብልጽግና ዘመን አሳልፏል፤ አንዳንዶቹም በመንግሥትና በጦር ሠራዊት ውስጥ ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ ደርሰዋል። እንዲሁም ላበረከቱት አገልግሎት የምስጋና መግለጫ ይሆን ዘንድ የርስት መሬት ተሰጥቷቸው ነበር። ከ1769 ጀምሮ ግን በሰለሞናዊው መንግሥት ውስጥ የነበረው ማዕከላዊ ሥልጣን በእጅጉ እየተዳከመ መጣ። ይህም በጸጥታው ረገድ አለመረጋጋትን ከመፍጠሩም በላይ፣ በጎንደር የነበረውን የግንባታ እንቅስቃሴና የማኅበረሰቡ አባላት በዚህ የሥራ መስክ የመሰማራት ዕድላቸውን አጥብቦታል።
እ.ኤ.አ. 1888–1892 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ አሰቃቂ ከሆኑት አደጋዎች አንዱ ተከስቶ ነበር፤ ይህም በቤተ እስራኤል ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። ይህ ወቅት "ክፉ ቀን" ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ጊዜ የተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችና ጦርነቶች ለከፋ ረሃብና ወረርሽኝ ምክንያት ሆነዋል። በወቅቱ የነበረው መጠነ-ሰፊ እልቂት በቤተ እስራኤል ላይ ያደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ፣ ከግማሽ እስከ ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው የማኅበረሰቡ አባል በዚህ ወቅት እንደተቀጠፈ ይገመታል።
በማኅበረሰቡና በሰፊው የዓለም ይሁዳውያን መካከል የተፈጠረው ግንኙነት።
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ በ15ኛው እና በ16ኛው ክፍለ ዘመን በግብፅ እና በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ይሁዳውያን በጻፏቸው ደብዳቤዎች ወደ ግብፅ እና ወደ እስራኤል ምድር ስለመጡ የኢትዮጵያ ይሁዲዎች ተጠቅሷል። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ እንደ መንገደኞች (ነጋዴዎች) ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ የጦር ምርኮኞች ነበሩ።
ለባርነት ተሽጠው ወደ ግብፅ የመጡት የኢትዮጵያ ይሁዲዎች በግብፅ የነበሩ የይሁዳውያን ማኅበረሰብ ዘንድ ስለ ቤተ እስራኤል ሃይማኖታዊ ማንነት እና ሁኔታ ሰፊ ክርክር አስነስተው ነበር፤ ይህም የሆነው በይሁዳውያን ሕግ መሠረት ይሁዳዊ ምርኮኞችን የመታደግ እና (የመዋጀት) ግዴታ ስላለ ነው። በዚያን ጊዜ የግብፅ ይሁዳውያን የበላይ መሪ የነበሩት ረቢ ዳዊት ቤን ዘምራ (ራድባዝ)፣ የኢትዮጵያ ይሁዳውያን ይሁዳዊነት እውቅና በመስጠት የሰጡት ውሳኔ፣ ከብዙ ዘመናት በኋላ ረቢ ዖቫዲያ ዮሴፍ የማኅበረሰቡን ይሁዳዊነት እውቅና በሰጡበት ታሪካዊ ደብዳቤያቸው እንደ መነሻና እንደ ዋቢ አገልግሏል።
በኢትዮጵያ ይሁዲዎች እና በሰፊው የይሁድ ዓለም መካከል ያለው ግንኙነት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ እንደገና መመዝገብ ተጀመረ። በዚያው ክፍለ ዘመን በ1840ዎቹ ዓመታት፣ ፈረንሳዊው ተመራማሪ አንቷን ዲአባዲ ባደረገው ግንኙነትና በወቅቱ የማኅበረሰቡ ከፍተኛ የሃይማኖት መሪ በነበሩት በአባ ይስሐቅ እና በደቀ መዝሙራቸው ጸጋ አምላክ እንዲሁም በጣሊያናዊው ይሁዲ ምሁር ኦሄቭ-ጌር ሉጻቶ መካከል የደብዳቤ ልውውጥ ተካሂዶ ነበር። በ1855 ዓ.ም የማኅበረሰቡ አባል የሆኑት ዳንኤል ቤን ኻናንያ ከልጃቸው ጋር ወደ ኢየሩሳሌም በመምጣት በከተማዋ ከሚገኙት የይሁዳውያን ማኅበረሰብ ጋር ለጥቂት ወራት ቆይተዋል።
በ1860 ዓ.ም በኢትዮጵያ ውስጥ የፕሮቴስታንት ሚሲዮን ተመሠረተ። ዓላማውም እዚያ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትን ይሁዳውያንን በመስበክ ወደ ክርስትና መለወጥ ነበር። ሚሲዮናውያኑና ወደ ክርስትና የተለወጡት ሰዎች ከማህበረሰቡ መንፈሳዊ መሪዎች ጋር ግጭት ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ ማህበረሰቡ መስዋዕት የማቅረብ መብቱ በባለስልጣናት በኩል ለጊዜው እንዲገደብ ለማድረግም ችለዋል። ይህም በሃይማኖታዊ ቅርሱ ውስጥ ማዕከላዊ አካል ነበር።
በወቅቱ የነበረውን ቀውስ፣ የድነት ተስፋንና የኢየሩሳሌምን ናፍቆት መሠረት በማድረግ፣ በ1862 ዓ.ም በሃይማኖታዊ መሪው አባ መሃሪ መሪነት በርካታ የማህበረሰቡ አባላት ወደ እስራኤል ምድር ጉዞ ጀመሩ። በጉዞው ላይ ብዙዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን የተረፉትም ወደ መኖሪያቸው ተመለሱ። ይሁን እንጂ ጉዞው ወደ የታሰበበት ግብ ላይ ባይደርስም፣ የማህበረሰቡ ለኢየሩሳሌም ያለውን ጥልቅ ናፍቆትና ይህም ናፍቆት በምኞት ብቻ ሳይሆን ልዩ በሆኑ ተግባራት ጭምር የሚገለጽ መሆኑን የሚያሳይ እስከ ዛሬ ድረስ የሚጠቀስ ትልቅ ምልክት ነው።
ከኢትዮጵያ ይሁዳውያን ጋር ያለው ግንኙነት መታደስና የሚሲዮናውያን በእነሱ ላይ በኃይል መንቀሳቀስ፣ የዓለም አይሁዳውያን ወደ እነሱ ልዑካንን እንዲልኩ አድርጓል። የመጀመሪያው ልዑክ በ1867 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1875) ዮሴፍ ሀሌቪ የተባሉ ልኡክ ተላከ። ከእሳቸው በኋላ፣ ከ30 ዓመታት በኋላ ደግሞ ሕይወቱን ለኢትዮጵያ ይሁዳውያንና ለዓለም ይሁዳውያን ግንኙነት አሳልፎ የሰጠው ተማሪው ያዕቆብ ፋይትሎቪች ተላከ። የነዚህ ልዑካን እንቅስቃሴ ዓላማ ስለ ኢትዮጵያ ይሁዳውያን መረዳት፣ የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ፣ የሚሲዮናውያንን ተፅዕኖ መከላከልና የትምህርት መሠረተ ልማቶችን ማመቻቸት ነበር።
ምርጥ የሆኑ የኢትዮጵያ አይሁዳውያን ወጣቶች በአውሮፓ እንዲማሩ በማለት ከኢትዮጵያ ተወሰዱ። ከዚያም በኋላ ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ በኢትዮጵያ መንግሥትና በማኅበረሰባቸው ውስጥ ተመድበው ሠርተዋል። ከእነዚህም መካከል እንደ ታምራት አማኑኤል፣ ጌጤ የርሚያስ፣ ዮና ቦጋለ እና ታደሰ ያዕቆብ ያሉትን መጥቀስ ይቻላል።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አስርት ዓመታት ውስጥ፣ በኢትዮጵያ ይሁዳውያንና በጽዮናዊያን አመራሮች መካከል ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ መጣ። በዚህም ምክንያት ለምሳሌ በ1950ዎቹ ሁለት የኢትዮጵያ አይሁዳውያን የሕፃናት ቡድኖች ወደ እስራኤል እንዲመጡ ተደረገ። የመጡበትም ዓላማ "ክፋር ባትያ" በተባለ የመሳፈሪያ (አዳሪ) ትምህርት ቤት ተምረውና ሰልጥነው ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በማኅበረሰባቸው ውስጥ መምህራን እንዲሆኑ ነበር። ሆኖም ግን፣ በኢትዮጵያ ይሁዳውያንና በእስራኤል መንግሥት መካከል የነበረው ግንኙነት እስከ 1970ዎቹ ድረስ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላውያን ወደ እስራኤል እስከመመለስ ደረጃ አልደረሰም ነበር።
ወደ እስራኤል አገር መግባት
በመዝሙራት፣ በጸሎቶች እና በዓመታዊው የስግድ (ምህልላ) በዓል ላይ እንደሚንጸባረቀው ሁሉ፣ በኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላውያን ዘንድ የጽዮን ናፍቆትና ምኞት ሁልጊዜም የነበረ ነው። ይህ ምኞትና ናፍቆት እ.ኤ.አ በ1862 (በፈረንጆች አቆጣጠር) አባ ማሐሪ በተባሉ መንፈሳዊ መሪ አማካኝነት፣ በርካታ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን ተሻግረው ወደ እስራኤል ለመመለስ ሙከራ እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል። ሆኖም ይህ ሙከራ እጅግ አሳዛኝና አስከፊ ውድቀት የገጠመው ነበር።
የእስራኤል መንግሥት ከመመሥረቱ ጥቂት ቀደም ብሎና ከተመሠረተ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ 10 ዓመታት ውስጥ፣ ጥቂት የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤል ቤተሰቦች ከየመን አይሁዳውያን ጋር በመሆን ወደ እስራኤል ገብተዋል። ይሁን እንጂ እስራኤል ራሷ አቅዳ ልታመጣቸው አልፈለገችም ነበር። ለዚህም ካቀረበቻቸው ምክንያቶች አንዱ "ይሁድነታቸው አልተረጋገጠም" የሚል ሲሆን፣ ይህም "የመመለሻ ሕግ" (ኾቅ ሃሹት) የኢትዮጵያ አይሁዳውያንን እንዳያካትት አግዶት ቆይቷል። በተጨማሪም በዚያ ወቅት የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላውያን በእስራኤል ምድር ከማኅበራዊና ከባህላዊ ሁኔታዎች ጋር መዋሃድ አይችሉም የሚሉ አመለካከቶች በመንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ ነበሩ።
የኢትዮጵያ ይሁዳውያን ወደ እስራኤል እንዲመጡ በሀገሪቱ ፍላጎት ባይኖርም፣ አልፎ አልፎ በግል ተነሳሽነት እንደ ቱሪስት ወይም ለሥራ በሚል ሰበብ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤል ወጣቶች ወደ እስራኤል ገብተዋል። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ እንደ አዲስ ገቢዎች (ኦሊም) እንዲቆጠሩ የሚያስችላቸውን "ጊዩር ለኹምራ" (የጥንቃቄ ጥምቀት) ሲያደርጉላቸው፣ የቀሩት ግን ያለ ህጋዊ ፈቃድ በእስራኤል በመቆየታቸው ከሀገር እንዲወጡ እና እንዲባረሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።
የኢትዮጵያ ይሁዳውያን በመንግሥት ላይ ብዙ ጫና ካደረጉ በኋላ፣ የቀድሞው የእስራኤል ዋና ሊቀ ራባናት ራብ ዖቫድያ ዮሴፍ "የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤል አይሁዳውያን ናቸው" የሚል ውሳኔ አስተላለፉ። ሆኖም መንግሥት ውሳኔውን ተቀብሎ ወዲያውኑ ተግባራዊ ለማድረግ አልፈለገም፤ አልተገበረውምም። እስከ 1975 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ድረስ የ"መመለሻ ህግ" የኢትዮጵያን ቤተ እስራኤል እንዲያካትት ቢደረግም፣ መንግሥት የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤልን ወደ እስራኤል ለማምጣት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሳያደርግ ቀጥሏል።
በመሆኑም እስከ 1977 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ድረስ በእስራኤል ውስጥ የነበሩት የኢትዮጵያ ይሁዳውያን ቁጥር 200 ብቻ ነበር። እነዚህ ጥቂት የማህበረሰብ አባላት የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤል እንዲመጡ ደብዳቤ በመጻፍ፣ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ፣ እንዲሁም ከእስራኤልና ከአለም አቀፍ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር በመገናኘት የማይታክት ጥረት አድርገዋል። በተጨማሪም አሜሪካዊው የረድኤት ድርጅት (AAEJ) ስለ ኢትዮጵያ አይሁዳውያን ሁኔታ በአለም መንግሥታትና በይሁዳውያን ዘንድ ግንዛቤ እንዲፈጠር አድርጓል።
የመንግሥት ሥልጣን የያዙት ጠቅላይ ምኒስቴር ምናኼም ቤጊን የኢትዮጵያ ይሁዳውያን ወደ እስራኤል ይመለሱ ዘንድ እንደ ዋና ግብ አድርገው በመቅረፃቸው የዓሊያ ትግሉ ፍሬ አፈራ። የመጀመሪያው ሙከራ የተደረገው በ1977 ሲሆን፣ ይህም በወቅቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባልነበራቸው በእስራኤል እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በተደረገ ሚስጥራዊ ስምምነት አማካኝነት ነበር። በስምምነቱ መሠረት እስራኤል ለኢትዮጵያ ወታደራዊ ድጋፍ እንድትሰጥ፣ በምላሹም ወደ 200 የሚጠጉ የኢትዮጵያ ይሁዳውያን ቤተሰቦችን መልሶ በማገናኘት ወደ እስራኤል እንዲገቡ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ነበር። ይሁን እንጂ 121 ሰዎች ከገቡ በኋላ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሼ ዳያን ስለ ስምምነቱ በሚዲያ ይፋ በማድረጋቸው ሂደቱ ተቋረጠ።
በ1979 ዓ.ም እንደ ፈረደ አኽሎም፣ ባሩክ ጠገኘ፣ ዝምና በርሀኑ እና ዘካርያስ ዮናስ ባሉ አንቀሳቃሾች እና በሞሳድ መካከል ግንኙነት ከተፈጠረ በኋላ ከኢትዮጵያ የሚደረገው ጉዞ (አሊያ) እንደገና ተጀመረ። በእነዚህ አንቀሳቃሾች አማካኝነት ለአዲስ የጉዞ መስመር መሰረት የተጣለ ሲሆን፣ በዚህም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የማህበረሰቡ አባላት ወደ ሱዳን የሚያደርጉትን እጅግ አድካሚ የእግር ጉዞ ጀመሩ፤ ከዚያም በምስጢር ወደ እስራኤል ገቡ።
ጉዞው ሳምንታትን አልፎ ተርፎም ወራትን የፈጀ ሲሆን፣ በጉዞው ወቅትም ተጓዦቹ ከመንግስት ወታደሮችና ከመንገድ ዘራፊዎች መደበቅ እንዲሁም አስቸጋሪውን መልክዓ ምድር፣ የውሃና የምግብ እጥረትን መቋቋም ነበረባቸው። ሱዳን ሲደርሱም ወደ እስራኤል የመሄድ ዕድል እስኪያገኙ ድረስ በስደተኛ ካምፖች ውስጥ ከወራት እስከ ዓመታት ለመቆየት ተገደዱ። በካምፖቹ ውስጥ ያለው የምግብና የንፅህና ሁኔታ በጣም ዝቅተኛ ነበር፤ ስደተኞቹም ከሱዳን ባለስልጣናትና ይሁዲ ካልሆኑ ስደተኞች የሚደርስባቸውን እንግልት ይታገሱ ነበር። ኢየሩሳሌም ለመድረስ ተስፋ ካደረጉት መካከል ብዙዎቹ በከባዱ ሁኔታ ተሸንፈው በጉዞ ላይ ወይም በስደተኛ ካምፖች ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ሕይወታቸውን አጥተዋል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ወደ 16,000 ሺህ የሚጠጉ ይሁዳውያ እስራኤል ሲደርሱ፣ ወደ 4,000 ሺህ የሚጠጉት ደግሞ በመንገድ ላይ እንደቀሩ ይገመታል።
የሱዳን የጉዞ መስመር ለ 10 ዓመታት ያህል ክፍት የነበረ ሲሆን፣ ይህም የተከናወነው በሞሳድ፣ በማህበረሰቡ አንቀሳቃሾች፣ በአየር ኃይል እና በባህር ኃይል ትብብር ነበር። ይህ ጉዞ የተለያየ መጠን ያላቸውን ዘመቻዎች ያካተተ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ትልቁ ሚብጻዕ ሙሼ "ኦፕሬሽን ሙሴ ወይም "ምጽአተ ሙሴ" (ከህዳር 12 ቀን 1977 እስከ ታህሳስ 27 ቀን 1977 ዓ.ም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር) ነበር። በዚህ ዘመቻ ከ6,000 በላይ ሰዎች ወደ እስራኤል የገቡ ሲሆን፣ ይህም በአሜሪካ አገናኝነት ከሱዳን መንግስት ጋር በተደረገ ምስጢራዊ ስምምነት የተከናወነ ነበር። ከአንድ ወር ተኩል በኋላ፣ የእስራኤል አካላት ስለ ዘመቻው መኖር ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ በማውጣታቸውና ይህም ለሱዳን ባለስልጣናት ትልቅ እፍረት በመፍጠሩ ምክንያት ዘመቻው ተቋረጠ። ይሁን እንጂ፣ በ1980ዎቹ ውስጥ አነስተኛ መጠን ያላቸው ዘመቻዎች ቀጥለው ነበር። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በእስራኤል የሚገኙ የማህበረሰቡ አንቀሳቃሾች መንግስት ቀሪዎቹን የኢትዮጵያ ይሁዳውያን ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት እንዳያቆም ግፊት ማድረጋቸውን ቀጠሉ።
ከነዚህም በተጨማሪ፣ በ80ዎቹ ውስጥ ሌሎች ትናንሽ ዘመቻዎች ተካሂደዋል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በእስራኤል የሚኖሩ ወገኖች፣ የእስራኤል መንግሥት የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላውያንን የማምጣት ጥረቱ እንዳይቀዘቅዝ ጫና ማድረጋቸውን ቀጥለው ነበር። በ1989 ዓ.ም (እ.አ.አ)፣ ከ10 ዓመታት መቋረጥ በኋላ እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አደሰች። ግንኙነቱ ከታደሰ በኋላም የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላውያን በቀጥታ ወደ እስራኤል መግባት ጀመሩ።
በእስራኤል የሚገኙ የቤተ እስራኤል አባላት እና የአሜሪካው AAEJ ድርጅት ባደረጉት ቅስቀሳ፣ በርካታ የኢትዮጵያ አይሁዳውያን መንደሮቻቸውን እየለቀቁ በአዲስ አበባ በሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ አካባቢ መሰብሰብ ጀመሩ።
በመጀመሪያ ላይ ወደ እስራኤል የመምጣቱ ሂደት በዝግታና በትንሽ ቁጥር ይከናወን የነበረ ሲሆን፣ ይህም በወቅቱ በእስራኤል ለነበሩት ቤተ እስራኤላውያን የሚያስደስት ነበር። በእስራኤል የነበሩት ወገኖች በሱዳን በኩል የነበረው የጉዞ መስመር ከተቋረጠ በኋላ፣ እዚያው የቀሩ ቤተሰቦቻቸው እንዲመጡና እንዲቀላቀሏቸው በመንግሥት ላይ ጫና ይፈጥሩ ነበር። በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት እየከፋ በመጣ ቁጥር፣ የኢትዮጵያ ይሁዳውያንን ለማምጣት የሚደረገው ጥረትም እየጠነከረ መጣ።
በመሆኑም መንግሥቱን የሚቃወሙ ታጣቂ ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ እየተቃረቡ በመምጣታቸው፣ በከተማዋ ተሰብስበው የሚገኙት ይሁዳውያን በአስቸኳይ ከቦታው እንዲወጡ የእስራኤል መንግሥት በሚያዝያ ወር 1991 ዓ.ም (እ.አ.አ) ውሳኔ አሳለፈ።
የእስራኤል መንግሥት ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከሞሳድ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከአይሁድ ኤጀንሲ (ሶህኑት) እና በእስራኤል ከሚኖሩ የቤተ እስራኤል ቀደምት ነዋሪዎች ጋር በመተባበር ፈታኝ የሆነውን የኢትዮጵያ ይሁዳውያንን የማምጣት ዘመቻ ዝግጅት ጀመረ። ይህ ዘመቻ "የሰለሞን ዘመቻ" (ኦፕሬሽን ሰለሞን) ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፣ ይሁዳውያን ከስደት ሀገር ወደ እስራኤል ከገቡባቸው ዘመቻዎች ሁሉ በታሪክ ትልቁ ተብሎ የሚታወቅ ነው። ዘመቻው በግንቦት ወር 1991 ዓ.ም (እ.አ.አ) ተጀመረ። በ36 ሰዓታት ውስጥ በተደረጉ 34 በረራዎች 14,000 አይሁዳውያን ወደ እስራኤል ገብተዋል። ከዚህ ዘመቻ በኋላ እስራኤል በ80ዎቹ ውስጥ በተቃዋሚዎች ምክንያት ለመግባት አስቸጋሪ ወደነበረው የቋራ አካባቢ ተወካዮቿን በመላክ፣ ከ1992 እስከ 1999 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ እስራኤል እንዲመጡ አድርጋለች።
ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የገቡትና እስከ አሁንም መግባታቸው የቀጠለው የመጨረሻዎቹ ቡድኖች "የእስራኤል ዘር" (ፈለስ ሙራ ወይም ቀሪ የኢትዮጵያ አይሁዳውያን ተብለው የሚታወቁት) ናቸው። የእነዚህ ሰዎች መሰረት ከቤተ እስራኤል ሆኖ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ ወደ ክርስትና የተለወጡ ናቸው። ይሁን እንጂ ክርስትናን ቢቀበሉም ከክርስቲያኑ ማህበረሰብ ጋር ሙሉ በሙሉ ሳይቀላቀሉ፣ በክርስትና እና በይሁዳውያን እምነት መካከል ባለ ሁኔታ ለብቻቸው የቆዩ ናቸው። አልፎ አልፎም ከቤተ እስራኤል ዘመዶቻቸው ጋር ማህበራዊ ግንኙነታቸውን ቀጥለው ነበር።
ይህ ማህበረሰብ በ"መመለሻ ህግ" (Law of Return) መሰረት ወደ እስራኤል መግባት ስለማይችሉ እና በሌላ በኩል ደግሞ በእስራኤል ውስጥ በርካታ ቤተሰቦች ስሏቸው መግባታቸው አከራካሪና አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።
በተጨማሪም የፈለስ ሙራ ማህበረሰብ ወደ እስራኤል ለመምጣት በሚጠባበቁበት እና በጉዳያቸው ላይ ውሳኔ እስኪያልፍ ድረስ የ"ጊዩር" (ወደ አይሁድ እምነት የመመለስ) ዝግጅትና ትምህርት ይከታተላሉ። ባለፉት ዓመታት አልፎ አልፎ በርካታ የእስራኤል ዘር ቡድኖች ወደ እስራኤል የገቡ ሲሆን፣ በዚህ መልክ እስካሁን 50,000 የሚሆኑ ሰዎች ወደ እስራኤል መጥተዋል። ይሁን እንጂ አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ እስራኤል ለመግባት የሚፈልጉ (የሚጠይቁ) በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ።
እስከ 2024 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ባለው መረጃ መሠረት፣ በእስራኤል የሚኖሩ የኢትዮጵያ ይሁዳውያን (ትውልደ ኢትዮጵያውያን) ማህበረሰብ ቁጥር ወደ 177,600 (መቶ ሰባ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ) ገደማ ደርሷል። ከእነዚህም መካከል 93,400 (ዘጠና ሦስት ሺህ አራት መቶ) የሚሆኑት በኢትዮጵያ የተወለዱ ሲሆኑ፣ 84,200 (ሰማኒያ አራት ሺህ ሁለት መቶ) የሚሆኑት ደግሞ በእስራኤል የተወለዱ ናቸው።
የቤት እስራኤል መንፈሳዊ መሪዎች
ካህናቶቻቸው (ቄሶቻቸው) እንደሌሎቹ አይሁዳውያን "ራባኒም" (ረቢዎች) ማለት ናቸው። በኢትዮጵያ በነበሩበት ጊዜ የቤተ እስራኤል መሪዎችና የኅብረተሰቡ የብርሃን ምንጭ ነበሩ። ሕገ ኦሪትና የኦሪት ትእዛዛት በእነሱ ዘንድ ነበሩ፤ ማንኛውም ሃይማኖታዊ ጉዳይ የእነሱ ኃላፊነት ነበር። በሚያስፈልግበት ጊዜ ሁሉ በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ተሰሚነትና ተፅዕኖ ነበራቸው። ያላቸው የኦሪትና የሥርዓት ዕውቀት በቤተ እስራኤል ማኅበረሰብ ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጭ የመሪነት ሥልጣን እንዲኖራቸው አድርጓል። በሰዎች መካከል አለመግባባት ሲፈጠርና በሽማግሌዎች መፈታት ሲያቅተው ነገሩ በቄሶች ይፈታ ነበር።
አንድ ቄስ የኦሪት ትምህርቱን የሚጀምረው በሰባት ወይም በስምንት ዓመቱ ነው። ትምህርቱን አጥንቶ እስኪመረቅ ድረስ እንደ አዳሪ ትምህርት ቤት በመነኮሳት ዘንድ ይቀመጣል። ትምህርቱን ካጠናቀቀና ካገባ በኋላ ነው ለቅስና የሚሾመው።
ከተሾመ በኋላ መንፈሳዊ መሪ እንዲሆን በማኅበረሰቡ ይመረጣል። የቄሶች መሪ የሆነው "ሊቀ ካህናት" በዚያ ክፍለ ሀገር ባሉ ቄሶች ሁሉ ይመረጣል። እርሱም የዚያ ክፍለ ሀገር ከፍተኛ መንፈሳዊ (ሃይማኖታዊ) መሪ ይሆናል።
ቄስ ድንግል የሆነችን ልጅ ነው የሚያገባው። በጣም ልዩና አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር ሚስቱን መፍታት አይችልም። ይህም ሊሆን የሚችለው ጉዳዩ ከፍተኛ ሥልጣን ባላቸው ቄሶች ተመርምሮ የቅስና ማዕረጉን የማይነካ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው። ሚስቱ የሞተችበት ቄስ ወጣትም ይሁን በዕድሜ የገፋ፣ ሊያገባ የሚችለው ድንግል የሆነችን ልጅ ብቻ ነው።
አንድ ቄስ በመነኮሳት ከተመረቀ በኋላ፣ በሚኖርበት መንደር በሚደረግ ሥነ ሥርዓት በታዋቂ ቄሶች ይሾማል። ብዙ ሕዝብ በሚገኝበት በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ በምግብ፣ በምርቃና በመዝሙር ይከበራል። በኢትዮጵያ ቤተ እስራኤል ዘንድ የቅስና ማዕረግ እጅግ የተከበረ ነው።
ቄሶች የመንደሩን ነዋሪዎች ይመራሉ፣ የዕለት ተዕለት ችግሮችንም በመመልከት ውሳኔ ይሰጡ ነበር። ተግባራቸውም ንጽህናን፣ ቅንነትን፣ ክብርንና ተገቢ የሆነ አካሄድን የተላበሰ ነበር።
በሚያገለግሉት ማህበረሰብ ውስጥ የአርአያነት ምሳሌዎች ናቸው።
ቀሶች እንደሌሎች ይሁዳውያን በግብርና አይተዳደሩም ነበር፤ ይህም ጊዜያቸውን ለኦሪት ትምህርት ይሰጡ ስለነበር፣ በማኅበረሰቡ አባላት በሚሰጡዋቸው በኩራትና በልገሳዎች እየተረዱ በትሕትና ይኖሩ ነበር። በእያንዳንዱ ትልቅ መንደር ቀሶች ነበሩ፣ እነርሱም በአቅራቢያቸው ለሚገኙ ትናንሽ መንደሮችም አገልግሎት ይሰጡ ነበር።
በቤታ እስራኤል ማኅበረሰብ ውስጥ ሌላው መንፈሳዊ የአመራር ሚና የመነኮሳት ነው። መነኮሳት ከማኅበረሰቡ ሕይወት ተለይተው በብቸኝነት ኦሪትን ለማጥናት ራሳቸውን የወሰኑ ሰዎች ናቸው። የሃይማኖት ምሥጢራት በእጃቸው ነበሩ፤ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰውም ቄሶችን ያስተምሩና ይሾሙ ነበር። መነኮሳት የኢትዮጵያ ይሁዳውያን ከፍተኛው መንፈሳዊ መሪዎች ነበሩ። በጸሎታቸውና በሕግጋታቸው ውስጥ ብዙ አስፈላጊ ገጽታዎችን ቀርጸዋል። አንዳንዶቹም እንደ ወጉ የትንቢት ደረጃ ደርሰው ነበር። ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አንስቶ የመነኮሳት ቁጥር እየቀነሰ ሄደ። መነኮሳት በማይገኙባቸው አካባቢዎችም ቄሶች የክህነት ትውልድን በማሰልጠንና በመሾም እንዲሁም የሃይማኖት መሪነትን በመያዝ ተግባራቸውን ተረከቡ።
መነኮሳት ጥብቅ የሆነ የንጽሕና ሕግ ይጠብቁ ነበር። ከሌሎች የማኅበረሰቡ አባላት ጋርም አካላዊ ግንኙነት ከማድረግ ይቆጠቡ ነበር። በክህነት ስልጠና ወቅት በእነርሱ ዘንድ ይማሩ የነበሩ ደቀ መዛሙርትም እንዲሁ ነበሩ። በማኅበረሰቡ ወግ መሠረት፣ መነኩሴ ሆኖ መሾም፣ ልክ እንደ ነቢይነት ሹመት፣ የሚሰጠው በእግዚአብሔር ነው። ለክህነት የሰለጠነ ደቀ መዝሙር፣ እግዚአብሔር መነኩሴ እንዲሆን ያዘዘው ከሆነ ከስልጠናው በኋላም በንጽሕናው ጸንቶ ይቆይና መነኩሴ ሆኖ ይሾም ነበር። በእግዚአብሔር መነኩሴ እንዲሆን ያልተመረጠ ደቀ መዝሙር ግን ስልጠናውን እንዳጠናቀቀ ወደ ማኅበረሰቡ ተመልሶ ቄስ ሆኖ ይሾም ነበር።